photo_2023-03-20_11-40-11

ኢትዮ አግሮ የመስኖ ስንዴ እና ቅመማ ቅመም ኤግዚቢሽን በይፋ ተከፈተ!!

መጋቢት 09/2015 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል በዛሬው ዕለት የተከፈተው «ኢትዮ አግሮ የመስኖ ስንዴ እና ቅመማ ቅመም ኤግዚቢሽን ለተከታታይ ሶስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን የተለያዩ መንግስታዊ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ እና የግል ድርጅቶች እና ማህበራት የተለያዩ ምርቶቻቸውን በማስተዋወቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን፣ ግብርና ሚኒስቴር እና ነጂብ አድቨርታይዚንግ ኤቨንት በቅንጅት እንዲዘጋጅ አድርገውታል፡፡
ኤግዚቢሽኑ በይፋ በተከፈተበት ወቅት ክቡር ዶ/ር አዱኛ እንደተናገሩት አገራችን ባላት ምቹ ስነምህዳር ከምታመርታቸው እና ወደ ውጭ ከሚላኩ የግብርና ምርቶች መካከል የቅመማ ቅመም ምርቶች ተጠቃሽ መሆናቸውን እና የበርካታ አርሶ አደሮች የኑሮ መሰረት፣ ለአገሪቱ ኢኮኖሚም የማይናቅ አስተዋጽዖ በማበርከት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡ ባለሥልጣን መ/ቤቱ ከተቋቋመ ጊዜ አንስቶ የቅመማ ቅመም ንኡስ ዘርፉን ከዘር ጀምሮ እስከ ኤክስፖርት ድረስ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት በርካታ ጥረቶች ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው በተኢለይም ግብይቱ በህግ እና በመመሪያ የተደገፈ እንዲሆን አድርጎ የአምራቹንም ሆነ አገሪቱ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ መመሪያ ተዘጋጅቶ መጽደቁን ተናግረዋል፡፡
ይህ ኤግዚቢሽንም ሲዘጋጅ በተለያየ ደረጃ በዘርፉ የተሰማሩ አርሶ አደሮች፣ ነጋዴዎች እና ላኪዎች ምርቶቻቸውን ለህብረተሰቡ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እና ቀጣይ የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንደሚያስችልም ነው የጠቆሙት፡፡
ክቡር አቶ አበራ ሙላት በግብርና ሚ/ር የክቡር ሚኒስትሩ ተወካይ በበኩላቸው አገራችን ባለፉት አምስት ዓመታት በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች ፈጣንና ዘላቂ ልማት ለማካሄድ እንዲሁም ከፍተኛ ዋጋ የሚያስገኙ የግብርና ምርቶች ወደ ማምረት ለማሸጋገር ስልት ተነድፎ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት የምርት ወጪን ለመቀነስ እየተደረገ ያለው ጥረትም ተጠናክሮ በመቀጠሉ በበጋ ስንዴ ልማቱ አመርቂ ውጤት በመምጣት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
ክብርት ወ/ሮ አለሚቱ ዑሙድ በሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚ/ር የሴቶች እና ህጻናት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ በበኩላቸው ይህ መድረክ በተለይም ሴቶች ተጠቃሚነታቸው እና የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው ከማድረግ አንጻር ያለው ፋይዳ በቀላሉ የሚታይ አለመሆኑን እና መድረኩን ላመቻቹ አካላትም ታላቅ ምስጋና እና አክብሮት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *