307981601_1592168747909052_199038549561629369_n

የአየር ንብረት ለውጥ በቡና ምርት ላይ የሚያስከትለውን ተጽእኖ ለመቋቋም እየተሰራ ነው!

የአየር ንብረት ለውጥ በቡና ምርት ላይ የሚያስከትለውን ተጽእኖ ለመቋቋም እየተሰራ ነው!

ለጫካ ቡና ልማት ትኩረት በመስጠት የአየር ንብረት ለውጥ በቡና ምርት ላይ የሚያስከትለውን ተጽእኖ ለመቋቋም እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ በቡና ጣዕም፣መጠንና ጥራት ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡

በኢትዮጵያም አየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን፤ ተግባራቱ በአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ የሆነውን የቡና ምርት ታሳቢ ያደረጉ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አዱኛ ደበላ የዓለም ሙቀት መጨመር ተወዳጅ የሆነውን የኢትዮጵያ አረቢካ ቡና ጣዕም፣መጠንና ጥራት ላይ አሉታ እንደሚያስከትል ነው ለኢዜአ የተናገሩት፡፡

ከዚህ አኳያ ቡናን በጫካ ውስጥ በጥላ ስር የማምረቱን ተግባር ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይ የቡና ልማትን ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በማስተሳሰር ይሰራል ነው ያሉት፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን የኢትዮጵያን የጫካ ቡና ዘረመል እንዳይጠፋ ሳይንሳዊ በሆነ አግባብ የማቆየት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

በተላይም የጫካ ቡናን የመጠበቅና የመንከባከብ ስራ በአሳታፊ የደን አስተዳደር ስልት በፕሮጀክት ተይዞ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከተለያዩ የዓለም አቀፍ ድርጅቶችን ጋር በመቀናጀት ቡናን ባለበት ለማቆየት ህብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የቡና አምራች አርሶ አደሮች ከሚያመርቱት ቡና ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ለአካባቢ ጥበቃ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ለአብነት ከሁለት ሄክታር በላይ ቡና ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች ያመረቱትን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችል የፖሊሲ ለውጥ መደረጉን አንስተዋል፡፡

በዚህም አንድ ሺህ የሚደርሱ አርሶ አደሮች ያመረቱትን ቡና ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚያስችላቸውን ፈቃድ መውሰዳቸውን ነው የተናገሩት፡፡

በቀጥታ ወደ ውጭ ገበያ በማቅረብ መሸጥ ያልቻሉት ደግሞ በህብረት ስራ ማህበር ተደራጀተው የሚያቀርቡበት አማራጭ ተዘርግቷል ብለዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የልዩ ጣዕም የጫካ ቡና አምራች አርሶ አደሮች ከዓለም ገበያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የገበያ ትስስር፣የማስተዋወቅና ሌሎች ስራዎች በመሰራቱ የቡና ምርትን ክብረ ወሰን በሆነ ዋጋ በመሸጥ ተጠቃሚ መሆን የጀመሩ አርሶ አደሮች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

የቡና ምርት ከኢትዮጵያ ህዝብ መካከል 16 በመቶ ለሚሆኑ ዜጎች የመተዳደሪያ ምንጭ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

አንድ ሆነን እንስራ ኢትዮጵያ ታሸንፍ !

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *