የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት!!

የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት!!
June 26, 2020 No Comments News admin

ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ በአዘጋጁ አገር የተመረቱ በጥራታቸው የላቁ ቡናዎችን ለመምረጥና ለመሸለም የሚካሄድ የላቀ የቡና ጥራት ውድድር ነው፡፡ ቀደም ሲል ውድድሩ ለሀያ አመታት በተለያዩ አገሮች ሲካሄድ የቆየ ቢሆንም በኢትዮጵያ ታሪክ ግን የመጀመሪያ ነው፡፡ ውድድሩን ለመጀመሪያ ጊዜ ስናካሂድ ቡናቸውን ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርገው በጥራት የሚያመርቱ ገበሬዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑና የተሻለ ዋጋ እንዲያገኙ ለማስቻል፣ አገሪቱም ያሏትን ሌሎች ያልታወቁ ምርጥ የቡና ዝርዎች ለማስተዋወቅ እንድትችል ነው፡፡ በዚህ ረገድ ካሰብነውም በላይ ተሳክቶልናል፡፡ ምንም እንኳ ውድድሩ የመጀመሪያ በመሆኑ እንዲህ አይነት ሰፊ ተሳትፎ ይገኝበታል የሚል እምነት ባይኖረንም፤ አርሶ አደሮቻችን ከውድድሩ በፊት የተሰጡትን ስልጠናዎች ፈጥነው በመረዳት በስፋት ሊሳተፉና ቀደም ሲል ባልታየ መልኩ 1459 የቡና ናሙናዎች ለውድድር ሊቀርቡ ችለዋል፡፡ እውነቱን ለመናገር ይህ የአገራችን ስም በከፍተኛ ደረጃ ከፍ ብሎ እንዲሰማ እድሉን የሰጠ ስለነበር ሁላችንም ኮርተናል፡፡ 
ውድድሩ ሲታሰብ እጅግ በደመቀ ሁኔታ ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ በኢትዮጵያ ውስጥ ለማካሄድ ነበር፡፡ ሆኖም ግን በአጋጣሚና ድንገት በተከሰተው የኮሮና ወረርሺኝ ምክንያት በመጀመሪያው ዙር ከተለዩት 150 ቡናዎች ውጪ ቀጣዮቹን ውድድሮች ለማካሄድ አልተቻለም፡፡ በዚህ ምክንያት የተመረጡትን ሳምፕሎች በከፍተኛ ጥንቃቄ ወደ አሜሪካን አገር ሊላኩ ችለዋል፡፡ በአሜሪካን አገር ውድድሩ ሲካሄድም እጅግ ዓለማቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ሲሆን ከመላው ዓለም ተውጣጥተው በብቃታቸው የተመሰከረላቸው ዳኞች የተሳተፉበት ነበር፡፡ 
ከውድድሩ ውጤት ሁላችንም እንደተረዳነው ለውድድር የቀረቡ ቡናዎች ሁሉ ለውድድር የሚመጥኑ እና ከፍተኛ አቅም ያላቸው ጥሩ ቡናዎች መሆናቸውን የተመዘገቡት ውጤቶች ምስክር ናቸው፡፡ በዛሬው እለት የተጠናቀቀውንም ዓለም አቀፍ የጨረታ ሂደት ሁላችንም በንቃት የተከታተልነው ሲሆን አሸናፊ ቡናዎች በፓውንድ ከ185.1 ዶላር ጀምሮ በየደረጃው ተሸጠዋል፡፡ አንድ ኪሎ ቡና በ407 የአሜሪካን ዶላር ወይም በ13ሺህ 838 ብር ማለት ነው፡፡ ጨረታው የተካሄደባቸው 28 ቡናዎች ደግሞ በአጠቃላይ 1ሚሊየን 348ሺህ 690 ዶላር የተሸጡ ሲሆን ይህም በካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ የቡና ጨረታ ውድድር ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነው ተብሎ ተመዝግቧል፡፡ ሁኔታው በእርግጥም ኢትዮጵያ የተለያዩ ዝርያ ቡናዎች መገኛ መሆኗን ለዓለም ሁሉ ለማሳየት መልካም አጋጣሚን የፈጠረ ሲሆን አዘጋጆቹም ሆኑ ሌሎች አካላት በቀጣይ ዓመታት በተደጋጋሚ ውድድሩን በኢትዮጵያ ውስጥ ለማካሄድ እጅጉን አበረታች እና መልካም አጋጣሚ መኖሩን ያረጋገጥንበት ነበር፡፡
በዚህ አጋጣሚም ተወዳዳሪዎቻችን በሙሉ፣ ውድድሩን በከፍተኛ ብቃት ያጠናቀቁትን አሸናፊዎች፣ ውድድሩን በብቃት የዳኙ ዳኞች እንዲሁም ውድድሩ ወደዚህ አገር እንዲመጣ ከእኛ ጋር በጥምረት ሲሰሩ የነበሩትን ፊድ ዘ ፊዩቸር ኢትዮጵያና ሌሎች አጋሮቻችንም በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ስም ከፍ ያለ ምስጋናዬን አቀርብላቸዋለሁ፡፡ በሚቀጥለው ዓመት በምናካሂደው ውድድር ላይ ከዚህ በበለጠ ዝግጀት እንደገና እንደምንገናኝም ባለሙሉ ተስፋ ነኝ፡፡
አመሠግናለሁ!!
አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር

Total Page Visits: 460 - Today Page Visits: 1
About The Author

Leave a reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *