የቅመማ ቅመም ስትራቴጅክ እቅድና ፕላትፎርም ላይ ምክክር ተካሄደ

የቅመማ ቅመም ስትራቴጅክ እቅድና ፕላትፎርም ላይ ምክክር ተካሄደ
January 4, 2021 No Comments News admin

በቢሾፍቱ ፒራሚድ ሪሶርት በቡና፣ ሻይ እና ቅመማ ቅመም ልማትና ግብይት ባለስልጣን የልማት ዘርፍ የተዘጋጀው ሁለት የአስር ዓመት የቅመማ ቅመም ስትራቴጂዎች ማለትም የቅመማ ቅመም ልማት ስትራቴጂ እና የቅመማ ቅመም ግብይት ስትራቴጂ ላይ የአንድ ቀን ወርክሾፕ ተካሂዷል፡፡ ከተለያዩ ክልሎች፣ ከፌዴራል እንዲሁም ከምርምር ተቋማት የተወከሉ የስራ ሃላፊዎችና ባለሙዎች ተሳትፈውበታል፡፡

ስብሰባውን የባለስልጣኑ መስሪያቤት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አዱኛ ደበላ በንግግር የከፈቱ ሲሆን በንግግራቸው የተጠራው የምክክር መድረክ ትኩረት የሚያደርገው ቅመማ ቅመም ላይ እንደሆነ አስገንዝበው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በዋናነት ቡና፣ ሻይ እና የቅመማ ቅመም ከልማቱ እስከ ግብይቱ በማሳለጥ ሃገራችን ኢትዮጵያ ከሶስት ዋና ዋና ምርቶች ጠቃሚ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንድትችል መስራት እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡ በማስከተልም ‹‹ሆኖም ከሶስት የግብርና ምርቶች የቅመማ ቅመም እምቅ አቅም እንደሀገር እንዳለ፤ ነገር ግን እንዳልተጠቀምን፤ ያልተጠቀምንበት ምክንያት ምንድነው በሚል ኮሚቴ ተዋቅሮ ተወያየወተንበታል ›› ብለዋል፡፡ ባደረጉትም ውይይት በዋናነት ከታዩት ችግሮች አንዱ አዋጅ፣ የግብይት ደንብና መመሪያ የሌለው መሆኑና ልማቱንም ግብይቱንም ለማስኬድ የአሰራር ስርዓት የሌለው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ እዚህ ለመድረስ ግን በስትራቴጂ ያሉትን ችግሮች በመለየትና በደረጃ በማስቀመጥ ቅድሚያ በዚያ ላይ መስራት ይገባል ብሎ በማመን የስትራቴጂ ዝግጅት ተጠናቆ በዕለቱ ለውይይት እንደቀረበ አስገንዝበዋል፡፡ በእለቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይተው በማጽደቅ እንደሀገር ጠቀሜታ ላይ እንደሚውልም ተናግረዋል፡፡ ከዋና ዳይሬክተሩ የእንኳን ደህና መጣችሁ የመክፈቻ ንግግር በኋላ ሶስቱ ሰነዶች የቀረቡ ሲሆን ከቀረቡት ሰነዶች መረዳት እንደተቻለው ስትራቴጂው መቀረጽ አስፈላጊነት ዘመናዊና ውጤታማ የምርምር እና የኤክስቴንሽን አሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት፣ ተስማሚ ቴክኖሎጂ ለማቅረብ እና የጥራት ቁጥጥር አሠራርና ስልት ነድፎ ለመተግበር፣ ዘመናዊ፣ ፍትሃዊና ህጋዊ የቅ/ቅመም ምርቶች የግብይት ሥርዓት ለመዘርጋት፣ በየደረጃው የሚናበብና የሚመጋገብ አደረጃጀት አሠራርና አመራር ለማስፈን የሚያስችል ቅንጅታዊ የአሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት መሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በቀረበው ስትራቴጂ ከ 2002 እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ በዋና ዋና ቅመማ ቅመም የለማ መሬት በሄክታር እና የተገኘ የምርት መጠን በቶን የቀረበ ሲሆን ከዚህም ማወቅ እንደተቻለው በ2010 በቅመማ ቅመም የተሸፈነው መሬት በሄክታር 200,000 (ሁለት መቶ ሺ) ሲሆን ምርቱ ደግሞ 350,000 (ሶስት መቶ ሃምሳ ሺ) ቶን መሆኑ ማወቅ ተችሏል፡፡ የስትራተጂው ራዕይ ‹‹በ2022 ኢትዮጵያ በቅ/ቅመም ዘርፍ በዓለም ከፍተኛ አምራችና ላኪ ሃገራት አንዷ ሆና ማየት›› እንደሆነና ተልዕኮው ደግሞ በቅ/ቅመም ሰብሎች ልማት፣ አግሮ ፕሮሰሲንግና ግብይት ሰንሰለት ያሉትን ተግዳሮቶችን በመለየት እንደሆነ ስትራቴጂው አስቀምጧል፡፡ በተጨማሪም የስትራቴጂው ግቦች ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ እሴት ጭመራ ማስፋፋትና ማሳደግ፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማሳደግ መሆኑ ታውቋል፡፡ በቅመማ ቅመም ልማት ስትራቴጂው ላይ እንደተቀመጠው አስከ 2017 ዓ.ም ድረስ 418 ሺ ሄክታር መሬት እስከ 2022 ድረስ ደግሞ 460 ሺህ ሄክታር ላይ ቅመማ ቅመም ለማምረት የታቀደ ሲሆን ምርቱም በቶን ሲታይ በቀጣይ አምስት አመታት ውስጥ 843 ሺህ ቶን፣ በቀጣይ አስር ዓመታት ደግሞ 1141 ሺህ ቶን ቅመማ ቅመም ለማምረት ታቅዷል፡፡ በቅመማ ቅመም ንግድ ስትራቴጂ ላይ እንደተቀመጠው ደግሞ ባለፈው ኣመት የቅመማ ቅመም የውጭ ንግድ በቶን 10000 (አስር ሺ ቶን) እንደነበረና ያስገኘው ገቢ በዶላር ሲሰላ 15000 ዶላር እንደነበር ማወቅ ተችሏል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ በየአመቱ ከምታመርተው የቅመማ ቅመም ምርት ውስጥ በአማካይ 3 በመቶ ብቻ ኤክስፖርት እየተደረገ እንደቆየ ተጠቁሟል፡፡ በጥሬው ተዘጋጀቶ የሚላከውን የቅመማ ቅመም ምርት መጠን በ2012 ከነበረበት 8.32 ሺህ ቶን እና 10.55 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በየዓመቱ አማካይ በመጠን 20.1%እና በገቢ 24.0% በማሳደግ በ2022 ዓም ወደ 39.8 ሺህ ቶን እና 90.35 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማድረስ ታቅዷል፡፡ ዕሴት ተጨምሮ የሚላከውን የቅመማ ቅመም ምርት መጠን ደግሞ በ2012 ዓም ከነበረበት 5.5 ሺህ ቶን እና ገቢ 5.47 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር አማካይ በዓመት በመጠን 15.8% እና በገቢ 24.1% በማሳደግ በ2022 ዓም ወደ 23.78 ቶን እና 47.53 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማድረስ ግብ ተጥሏል፡፡ በአጠቃላይ በ2012 ዓም ከነበረበት 11.9 ሺህ ቶን እና 16.02 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በአማካይ በየዓመቱ በመጠን 18.2% እና በገቢ 24.0% በማሳደግ በ2022 ዓም ወደ 63.59 ሺህ ቶን እና 137.88 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማድረስ ግብ ተጥሏል፡፡ ከጠቅላላ ምርት የኤክስፖርት ድርሻ በ2012 ከነበረው 3 በመቶ ድርሻ በ2022 ዓ.ም 12 በመቶ ለማድረስ ታቅዷል፡፡

Total Page Visits: 683 - Today Page Visits: 3
About The Author

Leave a reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *