ከፍተኛ ጥራት ያለውን ቡና በከፍተኛ ዋጋ እንዲገበያይ የሚያስችል የግብይት ሥርዓት ይፋ ተደረገ!!

ከፍተኛ ጥራት ያለውን ቡና በከፍተኛ ዋጋ እንዲገበያይ የሚያስችል የግብይት ሥርዓት ይፋ ተደረገ!!
May 31, 2021 No Comments News admin

ግንቦት 16/2013 ዓ.ምኢት/ቡ//ሻ/ባ

አርሶ አደሩ በጥራት ያዘጋጀውን ቡና በጥሩ ዋጋ ለመሸጥ የሚስችለውአዲስ የግብይት አሰራር በዛሬው እለት ይፋ ተደርጓል፡፡ በዛሬው እለት ይፋ የተደረገውና ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገው የቡና ግብይት ስርዓት (Micro Lot Coffee Trading Platform) የተሰኘ ሲሆን፤ ይህ አማራጭ ከእስከዛሬው የተለየና ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ የሚደረግ አሰራር ነው፡፡ ክቡር ዶ/ር አዱኛ ደበላ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር እና ክቡር አቶ ወንድማገኘሁ ነገራ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ስራ አስፈፃሚ በጋራ በመሆን በሂልተን ሆቴል በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው የግብይት ፕላት ፎርሙ ይፋ የተደረገው፡፡ ክቡር ዶ/ር አዱኛ በመግቢያ ንግግራቸው እንደገለጹት በቡና ስራ ለፍተው፣ ደክመው፣ ጥረው እና ግረው እየተጎሳቆሉም ቢሆን በቡና ላይ ተስፋ ባለመቁረጥ ቡናቸውን ለማቆየት የሚፍጨረጨሩትን አርሶ አደሮችን ሁኔታ መመልከት በየትኛውም ደረጃ የሚገኝን ዜጋ ስሜት መንካት ብቻ ሳይሆን በእጅጉ ልብን የሚሰብር ክስተት መሆኑን ተናግረው በተለይም የቡና አርሶ አደሮች የልፋታቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል በመንግስት ኩል በርካታ ስራዎች በመሰራት ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ አንጻር አርሶ አደሩ በቀጥታ ራሱ አምርቶ በጥራት ያዘጋጀውን ቡናን ወደ ውጭ እንዲልክ ከማስቻል ጀምሮ የተለያዩ የግብይት አማራጮች ተቀምጠውለት በሚመቸውና ያዋጣኛል በሚለው ሁኔታ እየሸጠ ተጠቃሚ በመሆን ላይ የሚገኝ ሲሆን ይህ በዛሬው እለት ይፋ የሚደረገውና በቅርብ ቀን የሚጀምረው የቡና ግብይት ስርዓት (Micro Lot Coffee Trading Platform) የቡና ግብይት አማራጭ ከእስከ ዛሬው የተለየ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ የሚደረግ አሰራር፣ መጠናቸው ዝቅተኛም ቢሆን በከፍተኛ ጥራት ተዘጋጅተው እና በላብራቶሪ ምርመራ ከ85 በመቶ እና በላይ የጥራት ደረጃ ውጤት የተሰጣቸውን የምርት ዱካቸው የሚታወቁ ቡናዎች የሚገበያዩበት አዲስ የአሰራር ሥርዓት እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ በዚህ አሰራር ለሽያጭ የሚቀርቡ ቡናዎችም ዋጋቸው እጅግ አማላይ የሆነና አርሶ አደሩንም ሆነ አቅራቢውን በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችለው አሰራር እንደሆነ አስረድተው አሰራሩ በተለይም የጥራት ደረጃቸው ከፍተኛ የሆኑ ቡናዎችን ለዓለም ገበያ በማቅረብ ተወዳዳሪ እንድንሆን እና በዋጋ የመደራደር አቅማችንንም በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመር የአገራችንን የውጭ ምንዛሬ ግኝት ከፍ የማድረግ ሚና እንደሚኖረው እና አርሶ አደሩንም ተጠቃሚ በማድረግ ገቢውን ከማሳደግ በተጨማሪ በርካታና አዳዲስ የውጭ ቡና ገዢ ድርጅቶች እና ድርጅቶችንም ትኩረት እንደሚስብ ተናግረዋል፡፡ክቡር አቶ ወንድማገኝ በበኩላቸው ለዚህ ግብይት የሚቀርብ ቡና በርካታ የተመሰከረላቸው ቡና ቀማሾች (Cuppers) በሚሳተፉበት የፓናል የላቦራቶሪ ምርመራ ደረጃ እንደሚሰጠው እና ምርቱም የሚቀመጠው ለዚሁ ተብሎ በተዘጋጀ ደረጃውን በጠበቀ ማከማቻ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ከንግድ ባንኮች ጋር በመረጃ መረብ የተያያዘ የክፍያና ርክክብ ሥርዓት እንዳላቸው የተናገሩት አቶ ወንድማገኝ በግብይት ማግስት አርሶ አደሮች ክፍያቸውን፤ ገዢዎችም ምርታቸውን እንዲያገኙ እንደሚደረግና የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ልዩ ግብይት (Micro Lot Trading) በከፍተኛ ዋጋ የሚከናወን ስለሆነ በአስተማማኝ የገበያ መረጃ ሥርዓት የተደገፈና ሁሉም የግብይት ተዋንያን ወቅታዊ መረጃ እንደሚያገኙበት አስረድተዋል፡፡ የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ግብይት የተሻለ ዋጋ የሚከፍሉ ተገበያዮች የሚመጡበት፤ የወጪ ንግዳችንን የሚያጠናክር፣ የአገራችንን ቡና ዓለም አቀፍ የገበያ እድሎችን የሚያሰፋ እንደሆነ፣ ይህን ግብይት ግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. በይፋ የሚጀመር መሆኑን፣ የሚጀመረውም ለባለ ልዩ ጣዕም ዓለም አቀፍ ውድድር (Cup of Excellence) ቀርበው በብሔራዊ ደረጃ አሸናፊ የሆኑትን አርሶ አደሮች ቡና በማገበያየት እንደሆነና ቡናዎቹ የሚገኙት ለውድድሩ ተብሎ በተዘጋጁ በአዲስ አበባ፣ በጂማና ሀዋሳ ባሉ ልዩ መጋዘኖች እንደሆነም ጨምረው ተናግረዋል፡፡

Total Page Visits: 429 - Today Page Visits: 3
About The Author

Leave a reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *