በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የቡና ማሰልጠኛ ማዕከል ተከፈተ!!

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የቡና ማሰልጠኛ ማዕከል ተከፈተ!!
June 8, 2021 No Comments News admin


ሰኔ 1/2013 ዓ.ም
የኢት/ቡ/ሻ/ባለስልጣን
በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን፣ በተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት /UNIDO፣ በጣልያን ትብብር ኤጀንሲ እንዲሁም ዓለማቀፍ ዝናን ያተረፈው ኢሊ ካፌ ትብብር በአገራችን የመጀመሪያ የሆነው የቡና ማሰልጠኛ ማዕከል ተከፍቷል፡፡
ማዕከሉ በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ህንጻ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን የባሬስታ ስልጠናን ጨምሮ በቡናው ዘርፍ በስልጠና የተደገፉ የተለያዩ ጥናት እና ምርምሮችም ይካሄዱበታል፡፡
ማዕከሉ ክቡር የግብርና ሚ/ር አቶ ዑመር ሁሴን፣ በኢትዮጵያ የጣልያን አምባሳደር ሚስተር አርቱሮ ሉዚል፣ የባለስልጣን መ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር አዱኛ ደበላ፣ ከተለያዩ የመንግስት መ/ቤቶች የመጡ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከ UNIDO፣ ከጣልያን ትብብር ኤጀንሲ እንዲሁም ከኢሊ ካፌ የመጡ በርካታ የስራ ኃላፊዎች እና እንግዶች በተገኙበት በይፋ ተመርቆ ተከፍቷል፡፡
ክቡር የግብርና ሚ/ር አቶ ዑመር ሁሴን በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ቡናን በዘመናዊ ሁኔታ ለመምራት፣ ደረጃውን ለማስጠበቅ እና ጥራቱ የተጠበቀ ምርት ለገበያ ለማቅረብ የማዕከሉ ሚና ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ አገራችን ከቡና የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ የዚህ ማዕከል መገንባት ወሳኝ እንደሆነ የጠቀሱት ሚኒስትሩ በዘርፉ የሚታየውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ችግር ለመቅረፍ እና በቡና ላይ ሰፊ የጥናትና ምርምር ስራዎች ለማከናወን ማዕከሉ ትልቅ አስተዋፅዖ ያደርጋል፡፡
ክቡር ዶ/ር አዱኛ በበኩላቸው የዚህ ማሰልጠኛ ማዕከል መከፈት በቡና እሴት ሠንሰለት ውስጥ ያሉትን ተዋናዮች የጋራ ግንኙነት የተጠናከረ ለማድረግ እና ዘርፉን ለማዘመን ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ በተነደፈው ስትራቴጂ መሰረት የታለመው ግብ ላይ ለመድረስ ከሚከናወኑ ተግባራት ይህ አንደኛው መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ ይህ እውን እንዲሆን ላደረጉ አካላት ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳ/ት በቦታው ተገኝቶ ዘግቦታል፡፡

Total Page Visits: 8698 - Today Page Visits: 15
About The Author

Leave a reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *