የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት

የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት
June 5, 2020 No Comments News admin


የኢትዪጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ከአሜሪካን ተራድኦ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ እንቅስቃሴ እንዲሁም ሌሎች አጋሮች ጋር በመተባበር በአለም ታዋቂ የሆነውን ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ የተባለውን የቡና ጥራት ውድድር ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ አምጥቷል ፡፡ ዉድድሩን ወደዚህ አገር ለማምጣት በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ ምክንያቱም ይህ በዓለም ታዋቂ የሆነ ውድድር ለቡና ዘርፉ በርካታ ጠቀሜታዎች እንደሚኖሩት ስለታመነበት ነው፡፡ ከዚህ በፊት የማይታወቁ የቡና ዝርያዎችን ለማግኘትና ለዓለም ለማስተዋወቅ ያስችላል፣ የተሻለ ጣዕም ያላቸውን ቡናዎችን በመምረጥ እውቅና ይሰጣል፤ በተሻለ ዋጋ ይሸጣል፣ አርሶ አደሩን እና በየደረጃው የሚገኘውን በቡና ዘርፍ የተሰማራ ዜጋ ሁሉ በየደረጃው ተጠቃሚ ያደርጋል፣ የአገርን ኢኮኖሚ ያሳድጋል እንዲሁም ለኢትዮጵያ ልዩ ቡናዎች በአለም በርካታ የገበያ ዕድሎችን ይፈጥራል፡፡
ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ባለፉት 20 አመታት በ 11 ቡና አምራች ሀገራት ተካሄዷል፡፡ ሆኖም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ባዘጋጀችው ውድድር 1459 የቡና ናሙናዎች ለውድድር ሊቀርቡ ችለዋል፡፡ ይህም በርካታ ቡና አፍቃርያንን እና ታዋቂ የዓለም ሚዲያዎችን ሁሉ ትኩረትን እንዲስብ አድርጎታል፡፡ በቡና መገኛነቷ በከፍተኛ ደረጃ ከምትታወቀው ኢትዮጵያ ለውድድር ቀርበው ከነበሩ 1459 የቡና ናሙናዎች ውስጥ በመጀመሪያው ዙር 150ዎቹ ተመራጮች ተለይተዋል፡፡ ሆኖም ከወቅቱ አስከፊ የበሽታ ወረርሺኝ ጋር በተያያዘ ቀጣዮቹን ውድድሮች በአገራችን ለማካሄድ ባለመቻሉ ሳምፕሎቹ ወደ አሜሪካን አገር ሊላኩ ችለዋል፡፡
ከዚያ በኋላ ከ150ዎቹ ተወዳዳሪ ቡናዎች መካከል 40ዎቹን ቡናዎች በብሄራዊ ደረጃ/National Stage ለመምረጥ የተካሄደው ፉክክር ከተጠበቀው በላይ ነበር፡፡ ለውድድሩ የቀረቡት ቡናዎች ጥራታቸው በእጅጉ የተመሰከረላቸው ቢሆንም ውድድር ነውና ዳኞች ለማበላለጥ እጅግ በተቸገሩበት ሁኔታ ሙያዊ የሆነ የየራሳቸውን ውጤት በመስጠት 40ዎቹ ቡናዎች ተለይተዋል፡፡ ይህም ውድድሩ ምን ያህል በከፍተኛ ፉክክር የታጀበ፣ የቀረቡት ቡናዎችም ለውድድር የሚመጥኑ እና ከፍተኛ አቅም ያላቸው ጥሩ ቡናዎች መሆናቸውን ማሳያ ምስክር ነው ፡፡
በስተመጨረሻም 28 ቡናዎች የ2020 ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ኤክሰለንስ ቤስት ቡናዎች ተብለው ከ87 ፐርሰንት በላይ ውጤት በማምጣት ሊመረጡ ችለዋል፡፡ 3 ቡናዎች ደግሞ 90 እና ከዚያ በላይ አምጥተው ድንቅ ቡናዎች ተብለው Presidential Award በሚል ከፍተኛ እውቅና ተሰጥቷቸው ተመርጠዋል፡፡ በእርግጥም ኢትዮጵያ የተለያዩ ዝርያ ቡናዎች መገኛ መሆኗን ለዓለም ሁሉ ለማሳየት የተወዳዳሪዎቹ ተሳትፎ ቁልፍ የነበረ ሲሆን አዘጋጆቹም ሆኑ ሌሎች አካላት በቀጣይ ዓመታት በተደጋጋሚ ውድድሩን በኢትዮጵያ ውስጥ ለማካሄድ እጅጉን አበረታች እና መልካም አጋጣሚ እንዳለ ያረጋገጡበት ሂደት ሆኗል፡፡ አጋጣሚው ኢትዮጵያ ምን ያህል የቡና አገር እንደሆነችና አቅምም እንዳላት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳየት ያስቻለ ነበር፡፡
የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ አሸናፊዎች እ.ኤ.አ June 25/2020 ለ24 ሰዓታት በሚቆይ ኦን ላይን ጨረታ የሚሸጡ ይሆናል፡፡ እውነቱን ለመናገር ውድድሩ ከዚህ በፊት እንደተገለጸው ሁሉ ደረጃውን የጠበቀ፣ ሙሉ እምነት የሚጣልበት እንዲሁም ደህንነቱን ጠብቆ የተከናወነ ነበር፡፡ ውድድሩን ሲዳኙ የነበሩትን የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ዳኞች በዚህ አጋጣሚ ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡
በመሆኑም በውድድሩ ላይ ተሳታፊ የነበሩትን አርሶ አደሮች፣ አልሚዎች፣ አቅራቢዎች፣ ማህበራት፣ የማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎች፣ ኤክስፖርተሮች እንዲሁም በዋናነት ውድድሩን በማዘጋጀትና በማስተባበር ከፍተኛ ሚና የነበራቸውን ፊድ ዘ ፊዩቸር ኢትዮጵያ ቫልዩ ቼይን አክቲቪቲ እንዲሁም አሊያንስ ፎር ኮፊ ኤክሰለንስ፣ ቡና አልሚዎች ማህበር፣ ቡና ላኪዎች ማህበር፣ ቡና አቅራቢዎች ማህበር፣ ቡና ቆዪዎች ማህበር፣ ዉመን ኢን ኮፊ፣ በዚህ ውድድር ላይ ቀጥተኛም ሆነ ቀጥተኛ ያልሆነ ሚና ለነበራቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ሁሉ የዚህ ታላቅ ስኬት ባለቤቶች ናቸውና በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ስም ከፍ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡
የውድድሩ አሸናፊዎች የራሳቸውን ብቻ ሳይሆን የአገራችንንም ስም በመላው ዓለም ከፍ ብሎ እንዲጠራ አድርገዋል፡፡ ውድድሩ ኢትዮጵያ ከቡና መገኛነቷም በላይ አዳዲስ እና ከዚህ በፊት ያልታወቁ ምርጥ ቡና ዝርያዎችም ባለቤት መሆኗንም ለዓለም ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል፡፡ ለዚህ ደግሞ ቡናቸውን በጥራት አምርተው ያቀረቡት ጀግና አርሶ አደሮች ባለውለታ ናቸው፡፡ ከዚህ ውድድር ሁሉም የአገራችን የቡና አርሶ አደሮች የተማሩት ነገር አለ፡፡ ” ጥራት ያሸልማል!!”፡፡ በመሆኑም ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገባችሁትም ሆነ በውድድሩ ላይ ለተሳተፋችሁ ሁሉ የላቀ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ 
ከዚህ በስተመጨረሻ ላይ ለመግለጽ የምፈልገው መንግስት የውጭ የግብርና ምርቶችን በተለይም ቡናን ለመደገፍ በከፍተኛ ደረጃ ቁርጠኝኘቱን እያሳየ እንደሚገኝ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ አሁን አለምን በከፍተኛ ደረጃ በማስጨነቅ ላይ በሚገኘው የኮሮና ወረርሺኝ ወቅት እንኳ ብዙ የወጪ ምርቶች ችግር ሲገጥማቸው ቡናችን በጥሩ ሁኔታ የውጭ ምንዛሬን አስገብቷል፡፡ ለዚህም መንግስት እንዲሁም ሁሉም በቡናው ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አካላት እያደረጉ በሚገኙት የተቀናጀ ጥረት ምክንያት ነው፡፡ ለወደፊቱም ይህ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነቴ ነው፡፡
ዓለማችንን የከበባትን የወቅቱን ችግር እጅ ለእጅ ተያይዘን እንደምናልፈው እና በሚቀጥለው ዓመት በምናካሂደው ውድድር ላይ ዳግም እንደምንገናኝም ባለሙሉ ተስፋ ነኝ፡፡

አመሠግናለሁ!!!

አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር

Total Page Visits: 575 - Today Page Visits: 3
About The Author

Leave a reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *