Uncategorized

በቡና አምራች ክልሎች ለሚገኙ የቡና ምርት ዝግጅትና ጥራት አጠባበቅ ባለሙያዎች የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጠ !

በቡና አምራች ክልሎች ለሚገኙ የቡና ምርት ዝግጅትና ጥራት አጠባበቅ ባለሙያዎች የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጠ !
(ኢ.ቡ.ሻ.ባ፣ ጥቅምት 20/ 2012 ዓ.ም) የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ከቡና አምራች ክልሎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በቡና ምርት ዝግጅትና ጥራት አጠባበቅ ላይ የተዘጋጀ የአሰልጣኞች ስልጠና ሰጠ፡፡
ስልጠናው ከጥቅምት 17 እስከ 20 ቀን 2012 ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ የተሰጠ ሲሆን ፣ ከጥቅምት 24 እስከ 27 ቀን 2012 ዓ.ም በጅማ ከተማ ይሰጣል፡፡ ከኦሮሚያ፣ ደቡብ ብ/ብ/ህዝቦች፣ ከአማራ እና ከጋምቤላ ክልሎች ከቡና ኩታ ገጠም ወረዳዎች የተውጣጡ 118 ባለሙያዎች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡
ከጥቅምት 17 እስከ 20 ቀን 2012 ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ የተሰጠውን ስልጠና በይፋ ያስጀመሩት በደቡብ ብ/ብ/ህ/ ክልል የቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ምርት ዝግጅትና የገበያ ልማት ምክትል ኃላፊ አቶ ሬድዋን ከድር ናቸው፡፡አቶ ሬድዋን

በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለፁት ቡና በሀገራችን የተወለደና እናት ሀገር እንሁን እንጅ ሀገራችንም ሆነ የዘርፉ ተዋናዮች ማግኘት የሚገባንን ጥቅም እያገኘን አይደለም ብለዋል፡፡ በዓለም ያሉ የቡና አምራች ሀገራት ከሚያመርቱት የምርት እና የግብይት አቅም አንፃር ሲነፃፀር ብዙ የሚቀረን ነው ያሉት አቶ ሬድዋን ተወዳዳሪ ለመሆን እስካሁን እንደ የኢትዮጵያ የቡናና ሻይ ባለስልጣን በርካታ ስራዎች የተሰሩና፣ እየተሰሩ ሲሆን አሁን ደግሞ ይህ ስልጠና የቡና ምርት ለሚሰበሰብበት ወቅት እጅግ ወቅታዊና ጠቃሚ ስልጠና በመሆኑ የባለስልጣን መ/ቤቱ በማዘጋጀቱ በክልሉ ስም ከልብ እያመሰገን ይህን የቡና ምርት አዘገጃጀትና ጥራት ስልጠና በትኩረት እንደምትከታተሉ በማመን ስልጠናው በይፋ መከፈቱን እየገለፅኩ ቡና ከፍተኛ ክትትልና እንክብካቤ የሚያስፈልገው ሰብል በመሆኑ የምርት አዘገጃጀት፣አያያዝና ጥራት አጠባበቁም በተሻሻሉ አሰራሮች ሊደገፍ ይገባል ብለዋል፡፡ይህ ከሆነ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ መሆን የሚችል ጥራቱን የጠበቀ ቡና አዘጋጅቶ በማቅረብ በዘርፉ የተሰማሩ ተሳታፊዎችንና ሀገሪቷን በሚጠበቀው ያህል ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል ብለዋል፡፡ በመሆኑም የሀገራችንን የምጣኔ ሀብት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ስልጠናው ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ስለሆነ በትጋት በመከታተል የበኩላችሁን እንድትወጡ ሲሉ ኃላፊው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የምርት ዝግጅትና አግሮ ፕሮሰሲንግ ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሞላ ደምሴ ስልጠናው በዋናነት በታጠበና በደረቅ ቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎች ምርት አዘገጃጀት ሂደት እና በቡና ምርት ዝግጅትና ጥራት አጠባበቅ ዙሪያ የሚሰጥ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ አቶ ሞላ አክለውም በስልጠናው ርዕሰ ጉዳዮች ስር የሚስተዋሉ ክፍተቶችን የሚቀርፍ የንድፈ ሀሳብ እና የተግባር ስልጠና የሚሰጥ ሲሆን በውጭ ገበያ በጥራት ተወዳዳሪ የሆነ ምርት እንዲቀርብ ማድረግ ዒላማው ያደረገ ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡ ከስልጠናው በኋላ የአርሶ አደሩና የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ የገቢ መጠን ማሻሻል፣የዘርፉ ባለሙያዎችም በተሻሻሉ የድህረ ምርት ቴክኖሎጅዎችንና የአሰራር ዘዴዎች ላይ በቂ ግንዛቤ በመፍጠር የማስፈፀምና የመፈፀም አቅማቸውን አድጎ ማየት እንዲሁም በቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎች የሚታየውን የቴክኒክ ክፍተት በመለየት ክህሎት መፍጠር የሚጠበቁ ውጤቶች መሆናቸውን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነትና የኮሚዩኒኬሽን ቡድን በቦታው ተገኝቶ ዘግቧል፡፡
ቡናን በመገኛ ሀገሩ አምርተን ዓለምን እናጠጣለን!

Add CommentYour email address will not be published

Shopping Cart