photo1698083785

በቡናው ዘርፍ የተሰማሩ ሴቶች /Women in Coffee ያዘጋጁት ዓለም አቀፍ ጉባዔ በአዲስ አበባ አካሄዱ

ጥቅምት 5፣ 2016
አዲስ አበባ፣
በቡናው ዘርፍ የተሰማሩ ሴቶች /Women in Coffee ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን እንዲሁም ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጁት 20ኛው ዓለም አቀፍ በቡናው ዘርፍ የተሰማሩ ሴቶች ጥምረት/International Women’s coffee Alliance ጉባዔ በአዲስ አበባ ከተማ ስካይ ላይት ሆቴል በመካሄድ ላይ ይገኛል!፡፡ በዚህ አለማቀፍ ጉባኤ ላይ ከከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተጨማሪ የተለያዩ አለማቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች፣  ከ33 ሀገራት የተውጣጡ በቡና ልማት የተሰማሩ ሴቶች እንዲሁም በእሴት ሠንሰለቱ የተሰማሩ ሴቶች፣ ቡና ገዥዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡


የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት ቡና ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ከመሆኑም ሌላ ለዜጎች ማህበራዊ ህይወት መጎልበት ያለው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ቡና ሲነሳ ከልማቱ ጀምሮ በየደረጃው ያለው የሴቶች ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት ክብርት ሚኒስትሯ ካለው የባህል ተጽዕኖ እና ሌሎች ጉዳዮች ምክንያት የተሳትፏቸውን ያህል እየተጠቀሙ እንዳልሆኑ ነው የገለጹት፡፡  ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከመሬት ባለቤትነት፣ ብድር አቅርቦት፣ መረጃ ወዘተ. አንጻር አሁንም ክፍተቶች ያሉ ቢሆንም እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችሉ የተለያዩ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ እና የህግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተው ተግባራዊ በመደረግ ላይ እንደሚገኙ እና ሌሎች የህግ ማሻሻያዎችም እንደተደረጉ ጠቁመዋል፡፡ ይህ የተዘጋጀ መድረክም በዘርፉ የተሰማሩትን ሴቶች ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ እና ሴቶችን በቡናው ዘርፍ የበለጠ ተሳታፊ እንዲሆኑ በማስቻል ተጨማሪ የገበያ እድሎች እንዲገኙ በማድረግ ረገድ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በተለይ ሴቶች የምርት ጥራታቸውን በማሳደግ ተወዳዳሪ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ ዶ/ር ኤርጎጌ በማጠቃለያ ንግግራቸው ላይ ሚኒስቴር መ/ቤታቸው የሚጠበቅበትን ድጋፍ በማድረግ በኩል የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግም ነው ቃል የገቡት፡፡
ክቡር ዶ/ር አዱኛ ደበላ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተርም በበኩላቸው የቡና መገኛ በሆነችው አገራችን በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው ይህ ዓለም አቀፍ የውመን ኢን ኮፊ ኮንቬንሽን መዘጋጀቱ ለሴቶች ብቻ ሳይሆን በዘርፉ ለተሰማሩ ሁሉ ልዩ ትርጉም እንዳለው ተናግረዋል፡፡ አጠቃላይ ከ70% በላይ የሚሆነው የቡና እሴት ሰንሰለት የሚሠራው በሴቶች መሆኑን እና በተለያዩ የአገራችን ቡና አብቃይ ክልሎች በችግኝ ማፍላት፤ መሬት በማዘጋጀት፤ በመትከል፤ በመንከባከብ፤ ፍሬውን በመሰብሰብ፤ በማጠብ፤ በማዘጋጀትና ወደ ገበያ በማቅረብ እንዲሁም ቡና በማፍላት እንደሚሳተፉ አስረድተዋል፡፡ ሆኖም በተጠቃሚነት ረገድ ከወንዶች ያነሰ ደረጃ ላይ ስለሚገኙ ይህንን ክፍተት ለመሙላት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥረት አስፈላጊ እንደሆነ አሳስበዋል፡፡
በኢትዮጵያ በተለይም እንደ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ሴቶች ከልማትም ሆነ ከገበያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ስትራቴጂ መዘጋጀቱን እና በዚሁ መሰረትም ከክልሎች፣ ከዞኖች፣ ከወረዳዎች፣ ከክልል ቡናና ሻይ ጽ/ቤቶች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ስትራቴጂውን ወደ ተግባር የማስገባቱ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ክቡር ዋና ዳይሬክተሩ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተነድፈው እየተተገበሩ መሆናቸውን እና ሴት አርሶ አደሮችና አብቃዮች ከሴቶች ላኪዎች ጋር በመገናኘት በግብይት ሂደቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱንም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡18:56

Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *