IMG_20240202_174344_848

አውሮፓ ህብረት በቅርቡ ተግባራዊ ይደረጋል ባለው መመሪያ (EUDR) ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተሰጠ!

 መድረኩ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ በማድረጉ የተለየ ያደርገዋል ተብሏል!!

(ጥር 23/2016 ዓ.ም፡ ኢ/ቡ/ሻ/ባ)፡-

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አውሮፓ በቅርቡ ተግባራዊ ይደረጋል ባለው መመሪያ (EUDR) ዙሪያ በስካይላይት ሆቴል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰጥቷል፡፡

መድረኩን በይፋ የከፈቱት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር አዱኛ ደበላ ናቸው፡፡ ዶ/ር አዱኛ በመክፈቻ ንግግራቸው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን ካስተላለፉ በኋላ በዛሬው ዕለት ለመገናኘታችን ምክንያት በቅርቡ እንዲተገበር በተፈለገው የአውሮፓ ህብረት የፀረ-ደን መመሪያ(EUDR)  ሰነድ ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ ነው ብለዋል፡፡ በመቀጠልም ዋና ዳይሬክተሩ የመመሪያውን አተገባበር በሚመለከት የተዘጋጀውን ብሔራዊ የትግበራ ዕቅድ ዙሪያ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን ዕቅዱም በገንዘብ ሚኒስቴር፣ በግብርና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በቅንጅት የተዘጋጀ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በመመሪያው ትኩረት ከተደረገባቸው የምርት ዓይነቶች አንዱ ቡና በመሆኑና ከ35 እስከ 40 በመቶ የሚሆነውን የውጪ ምንዛሪ የሚያመነጨውና ከ25 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ የሚያደርግ ምርት በመሆኑ ከመመሪያውና ከህብረቱ ሃገራት የገበያ ፍላጎት ጋር በማሰናሰን በተቻለ መጠን ትኩረት አድርገን ልንሰራበት ይገባል ሲሉ በአፅንኦት አሳስበዋል፡፡ 

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም በመድረኩ የሚገኙትን ገንቢ ግብዓቶችን በመጨመር በቀጣይ ለዲፕሎማቶችና ከፍተኛ የመንግስት አካላት ጉዳዩ የሚቀርብ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይህ EUDR 2013/1115 በመባል የተሰየመው መመሪያ ወደ ዘጠኝ ርዕሶች እና 38 የሚደርሱ የተለያዩ አንቀፆችን የያዘ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ዶ/ር አዱኛ አክለውም መመሪያው በዋናነት ካርቦን ልቀት መቀነስን፣ የጫካ ምንጣሮን መቀነስ እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መቀነስ አበይት ዓላማዎቹ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በዕቅዱ እንደተመለከተው የአውሮፓ ህብረት ገበያን መጠቀም የሚቻለው ምርቱ ከጫካ ምንጣሮ ነፃ ከሆነ፣ ከሀገሪቱ የአመራረት ህግጋቶች በመከተል የተመረተ ምርት ከሆነ እና በተፈለገው ስምምነት መልኩ ስለመተግበሩ ከተረጋገጠ ብቻ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ ይህ መመሪያ ሲተገበር ኢትዮጵያ ሊኖራት የሚችለውን ምቹ ሁኔታ እና ተግዳሮቶችን በዝርዝር አብራተዋል፡፡ በመድረኩ ከተለያዩ ፌዴራል ተቋማት፣ ከቡና አብቃይ ክልሎች፣ የቡና ማህበራት፣ የቡና አልሚዎች፣ ገዥ ወኪሎች፣ ዩኒዬኖች እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተገኝተዋል፡፡ 

በመጨረሻም ይህን መድረክ ለየት የሚያደርገው ሁሉም ተሳታፊ ዕቅዱን በመተግበር የበኩሉን የቤት ስራ የሚሰራበት በመሆኑ ነው ብለዋል- ዶ/ር አዱኛ ደበላ፡፡ ዶ/ር አዱኛ አክለውም መመሪያው ከአበይት ዓላማዎቹ አንፃር ቢታይ እጅግ የሚጠቅመንና ቡናችን የሚመለከቱ መረጃዎችን በውል እንድናውቀው የሚረዳን ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም መመረያው ሊሟላለት የሚፈልጋቸው ቅድመ ሁኔታዎችም በቡና ስራዎቻችን ልናደርገው በፈለግነውና በተሰሩ ስራዎች ዙሪያ ተጨባጭ መረጃዎች እንዲኖሩን ያስችላል ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡ መመሪያውን አለመተግበር በቀጥታ የቡና አልሚ አርሶ አደሩ ላይ ጫና ስለሚፈጥር በትኩረት ልንሰራበት ይገባል በማለት መደረኩ የተጠናቀቀ መሆኑን የባለስልጣን መ/ቤቱ የህዝብ ግንኙነትና የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቡድን በቦታው በመገኘት ዘግቧል፡፡ 

Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *