0.1

አርሶ አደር ላኪዎች የገበያ ትስስር መፍጠር በሚችሉበት እና የመደራደር አቅማቸውን በሚያሳድጉበት ቴክኒክ ዙሪያ ጠቃሚ ስልጠና ተሰጠ!!

ታህሳስ 24∕2016 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን፤ አርሶ አደር ላኪዎች አለማቀፍ የቡና ገበያውን መቆጣጠር እና የገበያ ትስስር መፍጠር በሚችሉበት እንዲሁም የመደራደር አቅማቸውን ማሳደግ በሚያስችላቸው ቴክኒክ ዙሪያ በሀዋሳ ከተማ ጠቃሚ ስልጠና ሰጥቷል∶∶ አርሶ አደሮቹ የተውጣጡት ከኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ እንዲሁም ማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ሲሆን ቁጥራቸው ደግሞ ከመቶ የሚልቅ ነው∶∶

ስልጠናውን በቦታው ተገኝተው የከፈቱት ክቡር አቶ መስፍን ቃሬ የሲዳማ ክልል ቡናና ፍራፍሬ ልማት ዋና ዳይሬክተር እንዲሁም ክቡር አቶ ሬድዋን ከድር የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቡናና ቅ∕ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ናቸው∶∶

ክቡር አቶ መስፍን ሰልጣኞችን እና ዝግጅቱን ያስተባበሩትን አካላት እንዲሁም አሰልጣኙን እንኳን ደህና መጣችሁ “ዳኢ ዊሾ“ ካሉ በኋላ፤ ቡና ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን ከፖለቲካዊ፣ አካባቢያዊ እንዲሁም ማህበራዊ ህይወት ጋር በቀጥታ የተቆራኘ ከመሆን ባሻገር የአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ግኝት መሰረት እና ኢትዮጵያ ካላት ህዝብ ቁጥር ሩብ ያህሉ የኑሮ መሰረት መሆኑን ባስተላለፉት መልእክት ገልጸዋል∶∶ ቀደም ባለው ጊዜ ቡና በቂ ትኩረት ስላልተሰጠው እና በበርካታ ውስብስብ ችግሮች የተጠላለፈ ቢሆንም አሁን ያለው መንግስት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ትኩረት በመስጠት የተለያዩ አዋጅ፣ ደንብ፣ መመሪያዎች እና የሪፎርም ተግባራት በመከናወናቸው አገሪቱም ሆነ አርሶ አደሩ የተሻለ ተጠቃሚ ቢሆኑም የታሰበው ደረጃ ላይ ለመድረስ የበለጠ ምርት እና ምርታማነትን መጨመር፣ ጥራትን መጠበቅ እንዲሁም የገበያ መዳረሻዎችን ማስፋት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል∶∶ ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ የመሰለ ውድድር በአገራችን መደረጉም በርካታ ሚሊየነር የቡና አርሶ አደሮችን መፍጠር እንዳስቻለና ከፍተኛ መነቃቃትንም እንደፈጠረ ተናግረዋል∶∶

ክቡር አቶ ሬድዋን በበኩላቸው  አርሶ አደር ላኪዎች በተፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ የላኪነት ፈቃድ አውጥተው በዚህ ደረጃ መገኘታቸው አስደሳች መሆኑን ጠቅሰው አገሪቱ ባስቀመጥችው ግብ መሰረት በ2022 በአለም 2ኛዋ ቡና አምራች አገር እንድትሆን ለማድረግ የአርሶ አደሩ ሚና ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል∶∶ ይህን ግብ ከዳር ለማድረስ ከፌዴራል ጀምሮ በየደረጃው ባለው የመንግስት እርከን ሰፊ  ስራ እየተሰራ እንደሆነና በቡና እሴት ሰንሰለቱ የሚገኙ ተዋናዮችም የየድርሻቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ጥሪ አቅርበዋል∶∶ ቡናችን ተፈጥሯዊ በመሆኑና የተፈጥሮ ማዳበሪያን ብቻ በመጠቀም የሚለማ በመሆኑ ሰፊ የገበያ እድል እንዳለው እና ጥራትን መጠበቅ እና ምርታማነትን ማሳደግ እስከተቻለ ድረስ እነብራዚል እና ኮሎምቢያ ተርታ ለመሰለፍ የሚያዳግት ነገር አለመኖሩን አስረድተዋል∶∶

ከሀላፊዎች መክፈቻ ስነስርአት በኋላ የአርደንት ኮፊ ማኔጂንግ ዳይሬክተር እና ባለቤት አቶ አሸናፊ አርጋው አለማቀፍ የቡና ገበያ ሁኔታ፣  ኢትዮጵያ ያላት የቡና መልማት ወርቃማ እድል፣ የገበያ ትስስርን እንዴት በቀላሉ መፍጠር ይቻላል?  የኮንትራት አፈጻጸም ዘዴ እንዲሁም አርሶ አደር ላኪዎቹ የመደራደር አቅማቸውን በሚያሳድጉበት ቴክኒክ ዙሪያ ረዘም ያለ፣ እጅግ ሳቢ እና ጠቃሚ ስልጠና ሰጥተዋል∶∶

ስልጠናው እንደተጠናቀቀ አርሶ አደር ላኪዎቹ በርካታ ሙያዊ ጥያቄዎችን አቅርበው ከመድረክ በቂ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው የተደረገ ሲሆን ይህን መሰል ህይወታቸውን መቀየር የሚያስችል ስልጠና በመሰጠቱ በእጅጉ መርካታቸውን እና ለሌሎችም መሰሉ እድል ሊመቻች እንደሚገባ ጠቁመዋል∶∶ ለዚህም ባለስልጣን መ∕ቤቱን እና አቶ አሸናፊን እጅግ ከልብ በመነጨ ስሜት አመስግነዋል∶∶

Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *