10-1

ተግዳሮቶች የተሻለ ጥረት ለማድረግ እና የመፍትሄ መንገድ ለማበጀት አይነተኛ ሚና እንዳላቸው ተገለፀ

ሚያዝያ 20∕2016 ዓ.ም
አዳማ

ተግዳሮቶች የተሻለ ጥረት ለማድረግ እና የመፍትሄ መንገድ ለማበጀት አይነተኛ ሚና እንዳላቸው ተገለፀ፤ቀሪ የቤት ስራዎች ቢኖሩም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሄደባቸው ርቀቶችም ሊደነቁ ይገባቸዋል ሲሉ የህዝብ ተወካዮች ም∕ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተናግረዋልⵑⵑ

ይህ የተገለፀው በዛሬው እለት የኢትዮጵያ ቡናና ባለስልጣን ባዘጋጀው እና የህዝብ ተወካዮች ም∕ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በተገኙበት የአውሮፓ ህብረት ባለፈው ሰኔ ባፀደቀው ቡናን ጨምሮ ከደን ጭፍጨፋ ነጻ የሆኑ ምርቶች መግዛት የሚል መመሪያ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ በተሰጠበት ወቅት ነው∶∶
የተከበሩ አቶ ሰለሞን ላሌ በህዝብ ተወካዮች ም∕ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እንደተናገሩት የአውሮፓ ህብረት ያወጣውን የEUDR መመሪያ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚተገብረው ቢገልፅም መሰል ተግዳሮቶች የተሻለ ጥረት ለማድረግ እና የመፍትሄ መንገድ ለማበጀት አይነተኛ ሚና ያላቸው በመሆናቸው የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመቋቋም ወደ እድል መለወጥ የሚቻልበት አጋጣሚም እንዳለ ነው የጠቆሙት∶∶
የተከበሩ አቶ ሰለሞን እንዳሉት መንግስት በስፋት እየሰራበት ካለው አረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ አንጻር በተለይም ቡና ከደኖች ጋር ተያይዞ የሚለማ በመሆኑ ለገዢዎቻችን በቴክኖሎጂ በተደገፈ ሁኔታ በማስተዋወቅ ከውጭ የሚመጣውን ጭና ለመቀነስ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል∶∶ በዚህ በኩል ከውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ጋር Parliamentary Diplomacy መስራቱ አይነተኛ አማራጭ እንደሆነ ጠቁመው ቡናና ሻይ ባለስልጣን መመሪያውን ለሁሉም ባለድርሻ አካላት በየደረጃው ማስተዋወቁ እና አገራዊ የድርጊት መርሀ ግብር ቀርፆ በስፋት እየሰራበት የሚገኝ በመሆኑ የሄደባቸው ርቀቶች ሊደነቁ ይገባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል∶∶ መመሪያውን ከመጪው የፈረንጆቹ ጥር ወር ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ አስቸጋሪ እና በቂ የዝግጅት ጊዜ የሚያስፈልግ በመሆኑ ህብረቱን በመንግስት በኩል በሚቀርብ ጥያቄ በቂ የእፎይታ ጊዜ እንዲኖር ለማድረግ አስፈላጊው ሁሉ ሊደረግ እንደሚገባ ሳይጠቁሙ አላለፉም∶∶

ክቡር ዋና ዳይሬክተር ዶ∕ር አዱኛ በበኩላቸው አጠቃላይ የመመሪያውን ይዘት በተመለከተ ሊያስገኛቸው የሚያስችላቸውን እድሎች እንዲሁም ተግዳሮቶቹን በስፋት አብራርተዋል∶∶ መመሪያውን የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ እንዳፀደቀው ለህብረቱ ዋና ፅ∕ቤት ከግብርና ሚ∕ር፣ ከገንዘብ ሚ∕ር፣ ከውጭ ጉዳይ ሚ∕ር እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የወጣው መመሪያ ሊያደርስ የሚችለውን ተፅዕኖ በመጠቆም ተገቢው ማስተካከያ እንዲኖረው ከማድረግ እና ጊዜውም በተቻለ መጠን ገፋ እንዲል በርካታ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን ጠቁመዋል∶∶ ጎን ለጎንም መመሪያውን ከአርሶ አደሩ ጀምሮ በየደረጃው ለሚገኙ መላው ተዋንያን ማስገንዘብ ሊደርስ የሚችለውን ተግዳሮት በብዙ መልኩ ሊቀርፍ ስለሚችል በስፋተ ሲሰራበት እንደቆየ አስረድተዋል∶∶


እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት በተለይ በአነስተኛ ማሳ ላይ ቡናውን ለሚያለማውን አ∕አደር ተፅዕኖው በቀላሉ የሚታይ አለመሆኑን የተናገሩት ክቡር ዋና ዳይሬክተሩ ከምንልከው ምርት ጀርመን፣ ቤልጅየምን እና ጣሊያንን ጨምሮ 30 በመቶ የሚሆነውን የኤክስፖርት ቡና የሚገዙት የህብረቱ አባለ አገራትንም ማጣት በፍጹም እንደማይገባ ነው ያብራሩት∶∶ ስለሆነም የሁሉንም መንግስታዊ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ ማህበራት፣ አለማቀፍ ድርጅቶች እንዲሁም መላው የቡና ማህበረሰብ አካላት ቅንጅት የሚጠይቅ በመሆኑ እርስ በእርስ በመደጋገፍ የተጠናከረ ስራ እንደሚጠይቅም አስምረውበታል∶∶


አውሮፓውያኑ የኢትዮጵያን ቡና እንደማጣፈጫ የሚጠቀሙበት በመሆኑ ያላቸውን ትስስር ማጣት ስለማይፈልጉ ሁል ጊዜም ክትትል እና ጥያቄያቸው እንዳልተለየ  የጠቆሙት ክቡር ዶ∕ር አዱኛ በነሱም በኩል ያለውን ጫና ማርገብ እንዲችሉ አስፈላጊውን ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን እና በአገር አቀፍ ደረጃ እየተከተልን ያለውን Green Legacy Initiative ከቡናችን ጋር ያለውን ቁርኝት በስፋት የማሳወቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረው አጠቃላይ የአገራችንን መመሪያዎች እና ህጎች ከህብረቱ ጋር በማጣጣም አስቻይ የድርጊት መርሀ ግብር ተቀርፆ እየተሄደበት እንደሆነም ተናግረዋል∶∶ በዚህ በኩል የፓርላማ አባላት ሚናም ቀላል ስላልሆነ የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል∶∶

Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *