308110053_456301133198970_5517434135114152517_n

የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ ችግረኛ ወገኖችን የምሳ ማብላት አከናወነ!!

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ አካባቢ የሚገኙ እና የመስቀልን በዓል ምክንያት በማድረግ ለ145 አቅመ ደካማ እና ሌሎች የጎዳና ተዳዳሪ ችግረኛ ወገኖች የምሳ ማብላት መርሃ ግብር ተካሂዷል።በመርሃ ግብሩ ላይ ክቡር ዶ/ር አዱኛ ደበላ የባለስልጣን መ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር፣ አቶ ሻፊ ዑመር ምክትል ዋና ዳይሬክተር፣ አቶ መሀመድ ሸምሱ የዋና ዳይሬክተር ጽ/ቤት ኃላፊን ጨምሮ ሌሎች የመ/ቤቱ መካከለኛ አመራሮች እና ባለሙያዎች ተገኝተውበታል፡፡

እነዚህ 145 የሚሆኑ እና ምንም ገቢ የሌላቸው ወገኖች በባለስልጣን መ/ቤቱ አካባቢ እና በክፍለ ከተማው የተለያዩ አካባቢዎች የተገኙ እንደሆኑ ክቡር ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ በተለያየ ምክንያት ኑሯቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ዜጎችን እና አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች አሁን ካለው የኑሮ ውድነት ለማላቀቅ እና በአገራችን ብቻ ሳይሆን መላውን ዓለም በማመስ ላይ የሚገኘውን የኑሮ ውድነት ለመከላከል እና ከችግሩ ለመላቀቅ መንግሥት በርካታ እንቅስቃሴዎች በማድረግ ላይ የሚገኝ መሆኑን የጠቀሱት ክቡር ዋና ዳይሬክተሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትም በየደረጃው እያከናወኑ የሚገኙት የማዕድ ማጋራት እንቅስቃሴም ኢትዮጵያውያን ምን ያህል በችግርም ሆነ በደስታ በአንድነት ለመቆማቸው ማሳያ እና ለነባር ማህበራዊ እሴታችን መገለጫ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

አሁን በባለስልጣን መ/ቤቱ የተካሄደው የማዕድ ማጋራት መርሀ ግብር ጅማሬ እንጂ ፍጻሜ እንደማይሆን የተናገሩት ክቡር ዶ/ር አዱኛ ለወደፊቱም መሰል ተግባራት ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ለማከናወን የታቀደ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ቀደም ሲል በደብረ ብርሀን ከተማ በጦርነት ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች የምግብ፣ ንጽህና መጠበቂያ እና አልባሳት ድጋፍ መደረጉ የሚታወስ ሲሆን በክፍለ ከተማው ለሚገኙ አካል ጉዳተኞች ድርጅት መሰል ድጋፍ መደረጉ አይዘነጋም፡፡

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *