u

ለአገሪቱ አራተኛ የሆነው የምርት ጥራት ምርምራ እና ሰርቲፊኬሽን ማዕከል በሀዋሳ ተከፈተ!!

ሚያዝያ 03 ቀን 2015 ዓ∙ም

ሀዋሳ

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በአዲስ አበባ አና ድሬዳዋ ከተሞች ብቻ ተወስኖ የቆየውን የምርት ጥራት ምርመራ እና ሰርቲፊኬሽን ማእከል በማስፋት በዛሬው እለት ደግሞ በአገሪቱ አራተኛ የሆነውን የምርት ጥራት ምርምራ እና ሰርቲፊኬሽን ማዕከል በሀዋሳ ከተማ አስመርቋል!!

በዚህ በዛሬው የምረቃ ስነስርዓት ላይ የተከበሩ አቶ ሰለሞን ላሌ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የግብርና እና አርብቶ አደር ጉዳዮች ቋሚ ሰብሳቢ፣ ክብርት ዶ/ር ሶፊያ ካሳ የግብርና ሚ/ር ሚኒስትር ዴኤታ፣ ክቡር አቶ ዑስማን ሱሩር የደ/ብ/ብ/ህ/ ክልል በምክትል ፕሬዝደንት ማዕረግ የግብርና እና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ፣ ክቡር ዶ/ር አዱኛ ደበላ የባለስልጣን መ/ቤቱ ዋና ዳ/ር እንዲሁም ክቡር አቶ መምሩ ሞኬ የሲዳማ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊን ጨምሮ ከፌዴራል፣ ከክልሎች፣ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ሌሎች ተቋማት ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

የተከበሩ አቶ ሰለሞን ላሌ በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ በባለፈው ሳምንት የጅማ ማእከል በይፋ ተመርቆ ስራ መጀመሩን አስታውሰው እና በዛሬው እለት ደግሞ የሀዋሳውን ማእከል በማስመረቅ ላይ በመገኘታቸው የተሰማቸው ደስታ የላቀ እንደሆነ ተናግረዋል፡ የነዚህ ማእከላት አገልግሎት መጀመር አርሶ አደሩንም ሆነ ሌሎች ተዋንያንን ከከፍተኛ ወጭ እና እንግልት ሊያድን የሚያስችል ከመሆኑም ሌላ በከፍተኛ ደረጃ በቡና አምራችነታቸው የሚታወቁትን ደቡብ እና ሲዳማ ክልሎች ጥራቱ የተጠበቀ ምርት አምርተው ኤክስፖርት እንዲያደርጉ የተሻለ እድል እንደሚያመቻችላቸው እምነታቸውን የገለጹ ሲሆን ይህ አገልግሎት ከመጀመሩ ጋር ተያይዞ የአካባቢው የልማት እንቅስቃሴ በበለጠ የሚነቃቃ ከመሆኑም ሌላ ለበርካታ ወጣቶችም ሰፊ የስራ እድል እንደሚፈጥርላቸው እምነቴ የጸና ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ከጥራት ምርመራ እና ሰርቲፊኬሽን አገልግሎት ጋር ተያይዞ አገልግሎቱን ከማቀላጠፍ በተጨማሪ የበርካታ ዜጎችንም ህይወት መለወጥ የሚያስችል ተግባር በመሆኑ በሌሎችም አካባቢዎች መስፋት ይኖርበታል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ክብርት ዶ/ር ሶፊያ እንደተናገሩት ምንም እንኳ ኢትዮጵያችን በርካታ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ክስተቶች እየተፈራረቁባት ቢፈትኗትም መንግስታችን ለብዙ ዘመናት በሀገራችን ላይ ተንሰራፍቶ የቆየውን ድህነት፣ ችግር እና በርካታ ፈተናዎች በመቋቋም በርካታ ለውጦች መታየታቸውን እና በግብርና ምርቶች ላይም የታየው ለውጥ አበረታች እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ የበጋ መስኖ ስንዴ አምርቶ ከፍተኛ መጠን ያለው ኤክስፖርት መደረጉ ትልቅ ስኬት እንደሆነ እና በቡናውም በኩል ላለፉት 4 አመታት እየተገኘ ያለው ገቢ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሬ በመደገፍ በኩል ያበረከተው አስተዋፅዖ ቀላል እንደማይባል ተናግረዋል፡፡ ይህን ግኝት የበለጠ ለማሳደግ ደግሞ የአርሶ አደሩን እና በየደረጃው የሚገኘውን ተዋናይ ተጠቃሚነት ማሳደግ አስፈላጊ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በሁለት ማእከላት ብቻ ተወስኖ ሲሰራ የነበረውን የምርት ጥራት ምርመራ እና ሰርቲፊኬሽን አገልግሎት በጅማ እና ሀዋሳ ከተሞችም ማስፋት መቻሉ ዘርፉን ከነበረበት ደረጃ አንድ እርምጃ ተጨማሪ ወደ ፊት የሚያስጉዘው ከመሆኑም ሌላ አርሶ አደሩንም ሆነ ሌሎች ተዋናዮች ከከፍተኛ እንግልት እና ወጪ የሚያድን በመሆኑ ሁሉንም ደስ ሊያሰኝ የሚችል ተግባር እንደሆነ እና ሚኒስቴር መ/ቤታቸውም ማእከላቱን ለመጠናከር የሚጠበቅበትን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነ ቃል ገብተዋል፡፡

ክቡር ዶ/ር አዱኛም እንዳሉት ማእከላቱን እዚህ ደረጃ እንዲደርሱ ለማድረግ በርካታ ውጣ ውረዶች እንደነበሩ እና ያለምንም ተጨማሪ በጀት ባለስልጣን መ/ቤቱ ያሉትን አቅሞች አማጦ እንደተጠቀመ እና በክልሎች እንዲሁም በውስን ባለሀብቶች በኩል በተሰጠ ተስፋ በድፍረት ሊገባበት እንደቻለ ጠቁመዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት ለቢሮ የሚሆን ቦታ እንደተገኘ፤ በመንግስት በኩል የመዋቅር ማስፈቀድ እና ሰራተኞች የመቅጠር ስራዎች፣ በዋናው መ/ቤት ከየቢሮ የነበሩ እንደ ወንበር፣ ጠረጴዛ፣ ሼልፍ ወዘተ ተሰባስበው፤ የተሰበሩት ተጠግነው ወደስራ እንደተገባ፣ በቂ ነው ባይባልም የላቦራቶሪ፣ የቅምሻ እና ሌሎች በርካታ ተጓዳኝ መሳሪያዎች ከውስጥ እና ከውጭ እንዲገባ መደረጉን፣ የስልክ፣ ዋይ ፋይ፣ መብራት እና ውሀም በክልሎቹ ቀና ትብብር እውን መሆኑን፣ ከዚህ ጎን ለጎን አዳዲስ ሰራተኞችን የማሰልጠን ስራ የተከናወነ መሆኑን እና የተለያዩ ቴክኒካዊ ስራ የሚሰራባቸወ ፎርማቶች እንዲታተሙ ተደርገው ለስራ ዝግጁ እንደተደረጉ አስረድተው ለዚህም ድጋፋቸው ላልተለየ የፌዴራል እና የክልል አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በእለቱ ለማእከሉ መቋቋም የላቀ አሰተዋፅዖ ለነበራቸው የክልል ተቋማት እውቅና እና ሽልማት የተሰጣቸው ሲሆን በቡና ጉንደላ ስራ ውጤት ላመጡ ሞዴል አርሶ አደሮችም በሞተር የሚሰራ መጋዝ ስጦታ በእለቱ የክብር እንግዶች ተበርክቶላቸዋል፡፡

Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *