በኢዩ ካፌ ፕሮጀክት አማካኝነት በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች በተመሳሳይ ሰዓት ለአምስት ቀናት ስልጠና ተሰጥቶ ተጠናቀቀ!!

ታህሳስ 22/2016 ዓ.ም

ኢ/ቡ/ሻ/ባለስልጣን

በኢ/ቡ/ ሻይ ባለስልጣን ኢዩ ካፌ ኘሮጀክት አማካኝነት የሚደገፈው የቡና አርሶ አደር መስክ ት/ቤት የሁለተኛ ዙር የአሰልጣኞች ስልጠና በሀረር፣ ጭሮ፣ ሻሸመኔ፣ ሶዶ፣ ሀዋሳ፣ ዲላ፣ ጅማ፣ አምቦ፣ መቱ፣ ቦንጋ፣ ሚዛን አማን፣ እንዲሁም ባህር ዳር  ከተሞች ሲሰጥ ቆይቶ በስኬት ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡ በነዚህ ከተሞች ሲሰጥ በቆየው ስልጠና ላይ የተለያዩ የየክልሎቹ የስራ ኃላፊዎች በመክፈቻ ስነስርዓቱ ላይ በመገኘት የእንኳን ደህና መጣችሁ እና መክፈቻ ንግግሮችን አድርገዋል፡፡

በአጠቃላይ ከኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ሲዳማ ክልሎች የተውጣጡ የቀበሌ እና ልማት ጣቢያ የተውጣጡ ከ500 በላይ ሰራተኞች ስልጠናውን የተከታተሉ ሲሆን ስልጠናው የተሰጠው ደግሞ በቡና አ/አደር ማሳ ት/ቤት/ CFFS በቂ ልምድ እና እውቀቱ ባላቸው ማስተር  እና ረዳት ባለሙያዎች አማካኝነት ነው፡፡

አጠቃላይ ስልጠናውን በተመለከተ ሲያስተባብሩ የነበሩት አቶ ፈቃዱ ደፈረስ በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልታን የቡና፣ ሻይና ቅ/ቅመም ኤክስቴንሽን መሪ ስራ አስፈጻሚ እንደተናገሩት ቀደም ሲል በቡናው ዘርፍ ላይ በነበሩ በርካታ ውስብስብ ሁኔታዎች አርሶ አደሩም ሆነ አገሪቱ ተጠቃሚ እንዳልነበሩ አስታውሰው፤ መንግስት በሰጠው ትኩረትና ተከታታይ እርምጃዎች ለባለፉት ተከታታይ ሶስት አመታት አጥጋቢ ውጤት መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡  ይህ ጅምር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ደግሞ ከአርሶ አደሩ ጀምሮ በየደረጃው የሚገኘው ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት እና ርብርብ ይጠይቃል፡፡

ይህን ውጤት ከማምጣት አንጻር ደግሞ ቁልፉ በአርሶ አደሩ እጅ መሆኑን እና ምርቱን በጥራት እና በመጠን ወደላቀ ደረጃ በማድረስ ግዴታውን መወጣት፣ ታሪኩንም መቀየር እንደሚኖርበት ተናግረዋል::  ከዚህ በመነሳት አሰልጣኞችም በእውቀት እና ክህሎት በመብቃት ስልጠናውን መሬት የማውረድ: ዘመናዊ አሰራሮች እና ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ አ/አደሩን ከዘልማድ አሰራር የተላቀቀ እንዲሆን በማድረግ በኩልም ትልቅ አገራዊ ሀላፊነት እንዳለባቸው አስረድተዋል::

በዚህ ረገድ የቡና አ/አደር ማሳ ት/ቤት/ CFFS በባለፈው አመት በቂ ስልጠና ከተሰጠ በኋላ በየወረዳዎቹ ተቋቁመው እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የነበሩ መሆናቸውን እና ይህንን ለማጠናከር ታስቦ በዘንድሮውም አመት ስልጠናው መዘጋጀቱን የጠቆሙት አቶ ፈቃዱ እንደታሰበውም ስልጠናው ላይ የተሳተፉት የልማት ጣቢያ ሰራተኞች በሙሉ ፍላጎት እና የነቃ ተሳትፎ ስልጠናውን ማጠናቀቃቸውን፣ በየአካባቢቸውም በሚመለሱበት ወቅት የቀሰሙትን እውቀት ሳይሰስቱ እንደሚያካፍሉ ቃል መግባታቸውንም ገልፀዋል፡፡

በመርሀ ግብሮቹ መሰረት ስልጠናዎቹ ለአምስት ቀናት በንድፈ ሀሳብና ተግባር ተደግፈው የቀረቡ ሲሆን የኢዩካፌ ፕሮጀክት አጠቃላይ ገፅታ የተመለከተ ሪፖርት ቀርቦ የጋራ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡ ሰልጣኖች በመጀመሪያ ዙር የሰለጠኑትን ስልጠና መሰረት በማድረግ በሁሉም ወረዳዎች እንዴት እንደተገበሩና ምን ውጤት እንዳስመዘገቡ በየቡድኑ ተወያይተው ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን በሪፖርታቸውም የሲኤፍኤፍ ማዕቀፍ ደረጃዎችን መሰረት በማድረግ እንደሰሩና አበረታች ውጤት እንዳስመዘገቡም ገልፀዋል፡፡ የሲኤፍኤፍ የትግበራ ደረጃዎችን በተመለከተ ውይይት የተካሄደ ከመሆኑም በላይ ውጤታማ የኤክስቴንሽን አገልግሎትና የሲኤፍኤፍ ጠቀሜታን በተመለከተ የተለያዩ ሰነዶች ቀርበው የቡድን ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡ ሰልጣኞችም የየአካባቢ ተሞክሯቸውን የተለዋወጡ ሲሆን በቡና አ/አደር ማሳ ት/ቤት/ CFFS በየወረዳዎቹ ምን እንደሚመስሉ በየቦታው በመገኘት ሰልጣኞቹ ተመልክተዋል፡፡

Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *