1

የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈረመ!!

ታህሳስ 10∕2016 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ከኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ጋር ከቅመማ ቅመም ጋር በተያያዘ በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ በዛሬው እለት ተፈራርሟል∶∶ በባለስልጣን መ∕ቤቱ በኩል ስምምነቱን የፈረሙት ክቡር ዋና ዳይሬክተር ዶ∕ር አዱኛ ደበላ ሲሆኑ ከኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት በኩል ደግሞ ዋና ስራ አስኪያጇ ክብርት ወ∕ሮ መአዛ አበራ ናቸው∶∶

ክቡር ዋና ዳይሬክተር ዶ∕ር አዱኛ በስምምነቱ ወቅት እንደተናገሩ ባለስልጣን መ∕ቤታቸው ከባለፉት ሶስት እና አራት አመታት ወዲህ በልማቱም ሆነ በግብይቱ በኩል ባከናወናቸው የሪፎርም ተግባራት ተጨባጭ ለውጦች እየታዩ እና በተለይም በቡና ኤክስፖርቱ ላይ ከፍተኛ እድገት እየታየ እንደሆነ ጠቁመዋል∶∶ በቡናው በኩል በባለስልጣን መ∕ቤቱ በኩል የጥራት ምርመራ እየተከናወነ ደረጃ ወጥቶለት እና የኦሪጅን ልየታ ተከናውኖ አይሲኦ ሰርቲፊኬት በመስጠት ወደ ተለያዩ አለም አገራት በመላክ ተወዳዳሪ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል∶∶

ዋና ዳይሬክተሩ በቴክኖሎጂው በኩል ሙሉ በሙሉ ዘመናዊ የሚባልበት ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚቀር ስራ ቢኖርም የጥራት ምርመራ ማእከላቱን በተለያዩ ክልሎችም የማስፋት ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል∶∶ ሆኖም በቅመማ ቅመም እና ሻይ ምርቶች ላይ የቅምሻ ማእከላት አለመኖራቸውን የጠቆሙት ክቡር ዶክተር አዱኛ በተለይም በቅ∕ቅመም የውጭ ንግድ በየአመቱ ከ20 ሚሊየን ዶላር ያላነሰ ገቢ እንደሚገኝ እና በዚህም 16 አይነት የቅመማ ቅመም አይነቶች እየተላኩ መሆናቸውንም አስረድተዋል∶∶ በተቋሙ የላቦራቶሪ መሳሪያዎች ባለመኖራቸው እና የተሟላ ቁሳቁስ ባለመኖሩ ለእነዚህ ምርቶች ደረጃ እንደማይወጣላቸውም ጨምረው ተናግረዋል∶∶ በመሆኑም ይህንን ችግር ለመቅረፍ ዘመናዊ መሳሪያዎች በተሟሉለት እና ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ምርመራ ከሚያደርገው ከኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ጋር በዛሬው እለት ይህንን የመግባባቢያ ስምምነት ለማድረግ መወሰናቸውን አስረድተዋል∶∶

ክብርት ወ∕ሮ መአዛ በበኩላቸው  የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ጋር በእንደዚህ አይነት ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ትልቅ አስተዋፅዖ ሊያደርግ በሚችል ምርት ላይ በጋራ መስራት የሚያስችል ስምምነት ላይ መድረሳቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል∶∶ ወ∕ሮ መአዛ እንዳሉት ድርጅቱ በዋናነት የሚሰጠው አገልግሎት የተስማሚነት ምዘና ሲሆን የተደራጁ የፍተሻ ላቦራቶሪዎች እንዳሏቸው እና ምርቶቹ በአገር አቀፍ ወይም በአለም አቀፍ ደረጃ በወጣላቸው ስታንዳርድ መሰረት የምርት ጥራቶቹን እንደሚያረጋግጡ ጠቁመዋል∶∶ ከዚያ በተጨማሪ የምርት ሰርቲፊኬሽን እንዲሁም የስራ አመራር ስርአት ሰርቲፊኬሽኖች እንደሚሰጡ አስረድተዋል∶∶ ይህን ተግባር በተቀናጀ ሁኔታ ከኤክስፖርተሩ ከውጭ አስመጪዎችኘ ለተቆጣጣሪ ተቋማት እንዲሁም ለአምራቾች እየሰጡ እንደሚገኙ ነው የጠቆሙት∶∶

በመሆኑም በፌዴራል ቡናና ሻይ ባለስልጣን በኩል ለውጭ ገበያ የሚላኩትን የቅመማ ቅመም ምርቶች አለማቀፍ ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ አስፈላጊውን ምርምራ በማከናወን ጥራቱን የተጠበቀ ምርት ለመላክ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል∶∶ ከዚህ በኋለ ቡድኑ ድርጅቱ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች እና አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ ተዘዋውሮ ጎብኝቷል∶  

Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *