IMG_20240602_124329_792

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በEU-Desira የቡና መፈልፈያ ማሽን ድጋፍ አደረገ።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በEU-Desira የኢትዮጵያ  ሴቶች ለቡና እና የአየር ንብረት የስፔን ትብብር ፕሮጀክት ለታቀፉ ወረዳዎች የቡና መፈልፈያ ማሽን ድጋፍ አደረገ።

የቡና መፈልፈያ ማሽኑ በየወረዳዎቹ ለሚገኙ ሴት አልሚዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ አለዉ ተብሏል።

(ግንቦት 26/2016 ዓ.ም: ኢ/ቡ/ሻ/ባ):- የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን  በEU-Desira የኢትዮጵያ ሴቶች ለቡና እና የአየር ንብረት የስፔን ትብብር ፕሮጀክት ለታቀፉ ወረዳዎች የቡና መፈልፈያ ማሽን ድጋፍ አድርጓል ።ድጋፉ የተደረገዉ በዋናነት በፕሮጀክቱ በታቀፉ ወረዳዎች ለሚገኙ ሴት አልሚዎች መሆኑን የባለስልጣን መ/ቤቱ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች አካትቶ ትግበራ ስራ አስፈፃሚ አቶ ፍፁም መንገሻ ገልፀዋል ።

አቶ ፍፁም በንግግራቸው እንደገለፁት ይህ ድጋፍ ሲደረግ የሴቶቹን ተሳትፎ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያደርስ ከመሆኑም በተጨማሪ የቡናን ምርት ጥራት በመጠበቅ ረገድ ያለዉ ጠቀሜታ ከፍተኛ ነዉም ብለዋል።ስራ አስፈፃሚው አክለውም በቡና ልማት እና ግብይቱ የሴቶች ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከመሆኑም በላይ በተለይም በምርት ጥራት አጠባበቅ ላይ የሴቶች ሚና ጎልቶ የሚታይ መሆኑን አብራርተዋል ።

ፕሮጀክቱ ተግባራዊ  ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ስራዎች እንደተሰሩ የገለፁት ኃለፊው በተለይም ለሴቶች ድጋፍ በማድረግና ተሳትፏቸዉን የበለጠ በማጠናከር፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በመስራት፣ የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት እና የጥናት ስራዎችን በማድረግና ከጥናት ግኝቱ በመነሳት ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ግብዓት የሚሆኑ አስተያየቶች ስለመላካቸዉና በተጨባጭ በርካታ ስራዎች የተሰሩ መሆኑን ገልፀዋል ። የሴቶችን ተጠቃሚነት ዕዉን ለማድረግ የሁሉንም አካላት ድጋፍ የሚጠይቅ ነዉ ያሉት ኃላፊዉ የፕሮጀክቱ መገባደጃ ጊዜ ከመቃረቡ አንፃር ስራዎችን በማስቀጠል በኩል በዞኖች እና ወረዳዎች የሚገኙት ተወካይ ባለሙያዎችና ሴት አልሚዎች ጥረት ሊቀጥል ይገባል ብለዋል። ሀገራችን ለቡና ልማት ያላትን ምቹነት ብሎም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ግምት ዉስጥ በማስገባት ከጫካ ቡና ጋር የተያያዘ የደን መመናመን እንዳይኖር ብሎም የአካባቢያዊ ስነምህዳሩን በመጠበቅ ተስማሚ የአየር ንብረት እንዲኖር በማድረግና የምግብ ዋስትናን በማሻሻል ረገድ ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርግ የነበረዉ  ይህ ፕሮጀክት በዘርፉ የሚታዩ በርካታ ማነቆዎችን በመፍታት ሀገሪቱ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም በተለይም የሴቶችንና ወጣቶችን ተጠቃሚነትና ተሳትፎ በማረጋገጥ በኩል በርካታ ስራዎችን መስራት ያስቻለ ነዉ ብለዋል።

ወ/ሮ ጥሩነሽ ፍሬሳ ፕሮጀክቱ ድጋፍ ካደረገላቸዉ የቡኖ በደሌ ዞን ጮራ ወረዳ ነዋሪና ሴት አልሚ አርሶ አደር ናቸዉ። ወ/ሮ ጥሩነሽ ስለተደረገላቸዉ ድጋፍ ከልብ አመስግነዉ በቀጣይ በትጋትና በኃላፊነት ቡናቸዉን ለማምረት የበለጠ ያነሳሳቸዉ ተግባር መሆኑን ገልፀዋል ።በኢሉ አባቦራ ዞን ያዮ ወረዳ ሴት ቡና አምራች የሆኑት ወ/ሮ ጥላዬ አለማየሁ በበኩላቸዉ በፕሮጀክቱና ባለስልጣን መ/ቤቱ ትብብር የሴቶችን ተሳትፎ ለማጠናከር የተደረገልን ድጋፍ ከፍተኛ በመሆኑ በኑሯችን ልንሻሻልና ህይወታችን ልንቀይር ያስችለናል ብለዋል።በተመሳሳይ በዚሁ ዞን ወ/ሮ ረጋቱ ጉተማ፣ ወ/ሮ ቢሻቄ ዓለሙ፣ ወ/ሮ ጥሩወርቅ ጠና እና ወ/ሮ ባሪቱ ደሳለኝ ከአለጌሰጫ ወረዳ ሞጉ ቀበሌ፣ ከዱራኒ ወረዳ ቦጮ ሶዮማ ቀበሌ፣ከቢሎኖጳ ወረዳ አገታ ቀበሌ እና ሁርሙ ወረዳ በተከታታይ ድጋፍ የተደረገላቸዉ ሴት ቡና አልሚዎች ናቸዉ። የተለያዩ መስፈርቶችን አሟልተዉ የተመረጡት ሴቶቹ ማሽኑ ጊዜያቸዉን መቆጠብ ከማስቻሉም በተጨማሪ የቡናቸዉን ጥራት የሚያስጠብቅና በገቢያቸዉ በኩልም ለዉጥ እንደሚያገኙበት ገልፀዋል።

ማሽኑ ሙሉ ለሙሉ ከብረት የተሰራና ጠንካራ ሲሆን  በገንዘብ ሲገመት በድምሩ ከ516ሺህ ብር በላይ የሚገመት ወጪ የተደረገበት መሆኑን መገንዘብ ተችሏል።ከድጋፍ መርሃግብሩ በኋላም የፕሮጀክቱን አፈፃፀምና የማህበረሰቡን ተሳትፎ በሚመለከት የሱፐርቪዥን ስራዎች ስለመሰራታቸዉ የባለስልጣን መ/ቤቱ የህዝብ ግንኙነትና የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ስራ አስፈፃሚ ቡድን በቦታዉ በመገኘት ዘግቧል።

Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *